Skip to Content

የራዕይ ትርጉም ምንድን ነው?

14 ኦገስት 2024
Squadwerk Innovations Pty Ltd
| No comments yet

የራእይ ትርጉም ምንድን ነው? ራእይ ማለት ዛሬ ላይ ቆሞ ነገን ማየት መቻል ነው። 

ዶክተር ማይልስ ራእይን እንዲህ ይገልጽዋል። “Vision is the glimpse of our future that God has purposed” - Dr. Myles Monroe


ራእይ እና ዐላማ የተያያዘ ነገር ነው። የተፈጠረበት ዐላማ የገባው ሰው በተፈጠረበት ዐላማ ውስጥ መኖር ይፈልጋል፤ ስለዚህ ምን ላድርግ ምን በህይወቴ ሰርቼ ልለፍ የሚል ጥብቅ ፍላጎት ያድርበታል፤ ስለዚህ ራእይ በተፈጠርንበት ዐላማ ውስጥ እንድንሰራው ከእግዚአብሔር የሚሰጠን ስራ ነው።

ራእይ በተለያየ ጊዜ ለተለያዩ ሰዎች በተለያየ ዘመን እና ቦታ እንዲፈፅሙት እግዚአብሔር የሚያሳያቸው ነገር ነው። ለምሳሌ፣ በሙሴ ዘመን የተገለጠለት የእግዚአብሔር ራእይ የእስራኤልን ሕዝብ ከግብፅ ባርነት ነፃ አውጥቶ ወተትና ማር ወደምታፈሰው ምድር ማስገባት ነበር። ለእርሱ የተሰጠው ስራ ደግሞ ከግብፅ የወጣውን ሕዝብ ማውረስ ነበር። ለነህምያ የተሰጠው ራእይ ደግሞ የፈረሰውን የኢየሩሳሌምን ቅጥር መስራት እና አምልኮን ማደስ ነበር። ስለዚህ ራእይ በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዩ ሰዎች የሚሰጥ የተለያየ ስራ ነው የምንለው።


ብዙ ሰዎች መሪዎችን ጨምሮ ምንድን ነው ራእያችሁ ሲባሉ ወንጌልን መስበክ ይላሉ፤ ይህ ተልኮ (mission) ነው እንጂ ራእይ (vision) አይደለም። ጌታ እናት የሰጠን ታላቁ ተልኮ የሁላችንም ስራ ነው፤ ራእይ ግን ከዛ የተለየ ነው። ስለዚህ (Purpose, Vision, Mission) ተለይቶ መታየት አለበት። ያለዚያ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያለው የተለየ ራእይ ሳንፈፅም እናልፉን። በሙሴ፣ በነህምያ፣ በእያሱ ወዘተ የተለያየ ነበር ራእዪ።


የጋራ ራእይ እና የግል ራእይ

ራእይ በሁለት ይከፈላል፤ የግል እና የጋራ ራእይ። የግል ራእይ ለህይወታችን ለቤተሰባችን የምንቀበለው ሲሆን የጋራ ራእይ ግን ለሕዝብ የምንቀበለው እና ከሕዝብ ጋር የምንሰራው ነው። የግል ራእይ በራሳችን ህይወት ዙሪያ ያተኮረ እኛ ብቻ አላፊነት ወስደን የምንፈፅመው ነው፤ ይህም የግል ንግድ (business) ቤተሰባችን ላይ ብቻ ያተኮረ አላፊነትና ባለቤትነት በእኛ ላይ የሆነ ሲሆን፣ የጋራ ራእይ ግን ህዝብ ላይ ያተኮረ፣ ባለአደራው ህዝብም የሆነበት፣ ህዝቡንም የሚያሳትፍ ነው። ለጋራ ራእይ ምሳሌ የሚሆነውን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመልከት።

ሙሴ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የጋራ ራእይን ከተቀበሉ ሰዎች አንዱ ነው።

ዘጸአት 3:3

"ሙሴም፡— ልሂድና ቍጥቋጦው ስለ ምን አልተቃጠለም ይህን ታላቅ ራእይ ልይ፡ አለ።"


4 እግዚአብሔር እርሱ ይመለከት ዘንድ እንደ መጣ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር ከቍጥቋጦው ውስጥ እርሱን ጠርቶ፡— ሙሴ፥ ሙሴ ሆይ፡ አለ። 5 እርሱም፡— እነሆኝ፡ አለ። ወደዚህ አትቅረብ፤ አንተ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ጫማህን ከእግርህ፡ አውጣ፡ አለው። 6 ደግሞም፡— እኔ የአባትህ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ፡ አለው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ያይ ዘንድ ፈርቶአልና ፊቱን ሸፈነ። 7 እግዚአብሔርም አለ፡— በግብፅ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፥ ከአስገባሪዎቻቸውም የተነሣ ጩኸታቸውን ሰማሁ፤ ሥቃያቸውንም አውቄአለሁ፤ 8 ከግብፃውያንም እጅ አድናቸው ዘንድ፥ ከዚያችም አገር ወተትና ማር ወደምታፈስሰው አገር ወደ ሰፊይቱና ወደ መልካሚቱ አገር ወደ ከነዓናውያንም ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም ስፍራ አወጣቸው ዘንድ ወረድሁ። 9 አሁንም እነሆ የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ወጣ፤ ግብፃውያንም የሚያደርጉባቸውን ግፍ ደግሞ አየሁ። 10 አሁንም ና፥ ሕዝቤን የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ታወጣ ዘንድ ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ።"


በዚህ ስፍራ እንደምናየው፣ እግዚአብሔር ነው ይህንን ራእይ ለሙሴ ሲያካፍለው የምናየው፤ ሙሴ ያለው አንድ ነገር ነው። ይህንን ታላቅ ራእይ ልይ፤ ራእይ እግዚአብሔር የሚያሳየንን ማየት ነው። እኛ ከልባችን የምናመነጨው አይደለም። ከዛ በኋላ እግዚአብሔር ለሙሴ በዝርዝር ሊሰራ የፈለገውን ለሙሴ አሳየው። የሚያስፈልገውን ሰው እና ማንኛውንም ነገር እንዳዘጋጀለት ነገረው። በዚያ ራእይ ውስጥ ጥበብና ማስተዋል የሞላባቸውን ሰዎች ሰጠው። ስለዚህ ራእዩን ሙሴ ቢቀበለውም፣ ሁሉንም የሚያሳትፍ የራእዩ ስራ ነው። ሌላ ምሳሌ ነህምያ ነው። እርሱም በተመሳሳይ ሁኔታ ራእዩን ቢቀበልም በስራው ላይ ህዝቡ ሁሉ የተሳተፈ ነው። ስለዚህ የጋራ ራእይ ሁላችንም ባለቤት የምንሆንበት እና የምንሳተፍበት ነው።

እግዚአብሔር ራእይን ሲሰጥ ለራእይ አስፈላጊ የሆነን ነገር ሁሉ ያቀርባል። ሙሴ ራእይን ሲቀበል ባስልኤልን እና ኤልያብን እና በጥበብ የሞሉ ፈታዮችን ሴቶች ሁሉ ሲሰጠው እናያለን።


ኦሪት ዘጸአት 36:1

"ለመቅደስም ማገልገያ ሥራ ሁሉ ያደርጉ ዘንድ እንዲያውቁ እግዚአብሔር ጥበብንና ማስተዋልን የሰጣቸው ባስልኤልና ኤልያብ፣ በልባቸው ጥበበኞችም ሁሉ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ነገር ሁሉ አደረጉ። 2 ሙሴም ባስልኤልንና ኤልያብን፥ እግዚአብሔርም በልቡ ጥበብን ያደረገለትን በልብ ጥበበኛ ሰው ሁሉ፥ ሥራውንም ለመሥራት ይቀርብ ዘንድ ልቡ ያስነሣውን ሁሉ ጠራቸው።"


ኦሪት ዘጸአት 35:25

"በልባቸው ጥበበኞች የሆኑ ሴቶችም በእጃቸው ፈተሉ፥ የፈተሉትንም ሰማያዊውን ሐምራዊውንም ቀዩንም ግምጃ፥ ጥሩውንም በፍታ አመጡ። 26 ልባቸውም በጥበብ ያስነሣቸው ሴቶች ሁሉ የፍየልን ጠጕር ፈተሉ።"


ነህምያ 2:8

"እንዲሁም ለንጉሡ ደን ጠባቂ ለአሳፍ፣ በቤተመቅደሱ አጠገብ ላለው ግንብ በሮች፣ ለከተማዪቱ ቅጥርና እኔም ለምገባበት ቤት ሠረገላ የሚሆን ዕንጨት እንዲሰጠኝ ደብዳቤ ይጻፍልኝ፤ መልካሚቱ የአምላኬ እጅ በእኔ ላይ ነበረችና ንጉሡም ፈቀደልኝ።"


የራእይ አፈፃፀም

2 እግዚአብሔርም መለሰልኝ፡ እንዲህም አለ፡ "አንባቢው ይፈጥን ዘንድ ራእዩን ጻፍ፥ በጽላትም ላይ ግለጠው። 3 ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፥ ወደ ፍጻሜውም ይቸኵላል፥ እርሱም አይዋሽም፤ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፤ እርሱ አይዘገይም።"


ራእዩ እንዲፈፀም በግልፅ ለአንባቢው ወይም ለራእዩ ተሳታፊዎች ግለጽ መሆን አለበት። የነህምያ መፅሐፍ በጣም ጥሩ የራእይን ፍፃሜ የምናይበት መፅሐፍ ነው፤ ሚስጥሩ ምንድን ነው ብለን ስንጠይቅ ነህምያ ራእዩን ከላይ ከአለቆች እስከታች ድረስ በግልፅ ምን ሆኔታ ላይ እንዳሉ መሰራት የሚገባውን ነገር በማሳየት ህዝቡን አንድ ሆኖ እንዲነሳ ያረገ መሪ ነው። መሪ መጀመርያ ማየት፣ ከዛ ማሳየት ከቻለ ራእዩ ወደ ፍፃሜ የማይመጣበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ዛሬ በዚህ ዘመን ያለው ችግር አንደኛው ባለራእይ ማጣት ሲሆን ሁለተኛው ራእዩን በግልፅ ለህዝብ አለማስተላለፍ ነው። ራእዩ በግልፅ ሲፃፍ አንባቢው ይፈጥናል፤ ራእዩም ወደ ፍፃሜው ይቸኩላል። ህዝቡን ባለራእይ ስናረግ ህዝቡ ለራእዩ ይጨክናል ይሰጣል፤ ህዝብ ራእይ ከሌለው ግን ራእይ ላይ ሳይሆን ባለራእይ ላይ ነው የሚጨክነው። በሙሴ የሆነው ያ ነው፤ ህዝቡ ምድረበዳ ለመቅረቱ ምክንያት በራሱ አንደበት መስክሯል። በነህምያ መፅሐፍ ግን የህዝቡ ልብ ለስራው ጨክኖ ይሰጣል። ህዝቡን ባለራእይ ስናረግ የእኔ የሚል ስሜት ይሰማዋል።


ምሳሌ 29:18

"ራእይ በሌለበት ሕዝብ መረን ይሆናል፤ ሕግን የሚጠብቅ ግን የተባረከ ነው።"


ራእይ የሌለው መሪ አይደለም የሚለው ራእይ የሌለው ህዝብ ነው የምንለው። ብዙ ጊዜ ባለራእይ ሲባል መሪን ብቻ ነው የምናስበው። ይህ ፈፀሙ የተሳሳተ እና ራእይ እንዳይፈፀም ዋና እንቅፉት የሚሆነው ጉዳይ ነው። ስለዚህ በአንድ ቦታ ራእይ ከሌለ መረንነት አለ፤ ሰው ሁሉ የፈለገውን ማረግ ይፈልጋል። ምክንያቱም በዛ ስፍራ ግልፅ የሆነ ራእይ የለም። ግልፅ የሆነ ራእይ ባለበት ስፍራ ግን የሚስብና ቅርፅ ያለው ነገር እናያለን። ስለዚህ ራእይን መቀበል አንድ ነገር ሲሆን ራእዩን ማካፈል እና ሌሎችን ባለራእይ ማረግ ደግሞ ሌላ ስራ ነው። አንድ ሰው የጋራ ራእይ ተቀብሎ ሰዎችን ባለራእይ ካላደረገ ያ ራእይ ተፈፀሚነት አይኖረውም። ምክንያቱም ያ ራእይ ተፈፀሚነት በህብረት ነው የሚያገኝው። በሰዎች ውስጥ ያለውን ፀጋ ማወቅ እና እያንዳንዱን በተሰጠው ፀጋ እንዲያገለግል ማነሳሳት የመሪው አላፊነት ነው። ስጦታዎች የተሰጡት ለአካሉ ጥቅም ነው። በነህምያ መፅሐፍ የምናየው አስደናቂ ነገር ያ ነው፤ እያንዳንዱ በስራው ላይ ተሳትፉለት። ልዮ ስጦታ ያላቸው በየቦታቸው መድቦ ህዝቡ ሁሉ በቅጥሩ ላይ ተበትነው በመስራት ራእዩ ወደ ፍፃሜ ሊደርስ ችሏል።


የራእይ እንቅፍቶች


ራእዩን በትክክል አለመረዳት። በንባቆም መፅሐፍ ላይ ራእዩን በግልፅ ጽፈው ይላል።

ራእዩ የሚያስከፍለውን ዋጋ አለማወቅ። ነህምያ፣ ዮሴፍ፣ ሙሴ ጥሩ ምሳሌዎቻችን ናቸው።

የራእዩን አፈፃፀም እና መርህ አለማወቅ። ነህምያ በመፀለይ ነው ሚስጥሩ የተቀበለው።

የእግዚአብሔር ቤት ቤተክርስቲያን ራእይ

የቤተክርስቲያኒቷ ራእይ “የእግዚአብሔር ህዝብ ካለበት መንፈሳዊ ጉስቁልና ወጥቶ ሙሉ ሰው ሆኖ ወደሚሰራበት እና በህይወት ወደሚበዛበት ማንነት ማድረስ ሲሆን ይህም በራሱ መናገር፣ ማየት፣ መስማት የሚችል አንድን ፍፁም ሰው መስራት ነው።

መጽሐፈ ነህምያ 2:17

"እኔም፡— እኛ ያለንበትን ጉስቁልና ኢየሩሳሌም እንደ ፈረሰች፥ በሮችዋም በእሳት እንደ ተቃጠሉ ታያላችሁ፤ አሁንም ከእንግዲህ ወዲህ መሳለቂያ እንዳንሆን ኑና የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንሥራ አልኋቸው።"


የዮሐንስ ራእይ 3:17

"ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ፥ ጉስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥"


መዝሙረ ዳዊት 119:92

"ሕግህ ተድላዬ ባይሆን፥ ቀድሞ በጉስቁልናዬ በጠፋሁ ነበር።"


ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1:28

"እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን፣ ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው። 29 ለዚህም ነገር ደግሞ፥ በእኔ በኃይል እንደሚሠራ እንደ አሠራሩ እየተጋደልሁ፥ እደክማለሁ።"


የዮሐንስ ወንጌል 9:20

"ይህ ልጃችን እንደ ሆነ፣ ዕውርም ሆኖ እንደ ተወለደ እናውቃለን፤ ዳሩ ግን አሁን እንዴት እንዳየ አናውቅም፥ ወይም ዓይኖቹን ማን እንደ ከፈተ እኛ አናውቅም፤ ጠይቁት እርሱ ሙሉ ሰው ነው፤ እርሱ ስለ ራሱ ይናገራል፡ አሉ።"


**ይህንን ራእይ በሰው ውስጥ ለማስረፅ በትምህርት፣ በውይይት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ በስነጽሁፍ እና በተለያዩ መንገዶች መስራት ይጠይቃል። እግዚአብሔር ያሳየንን ይህንን ራእይ ለመፈፀም በአመታት ውስጥ በታማኝነት ሲተጋ አይተነዋል። እግዚአብሔር ኤርምያስን ምን ታያለህ ብሎ ጠይቆ ያየው ትክክል እንደ ሆነ ሲያውቅ እፈፅመው ዘንድ እተጋለሁ እንዳለው፣ እኛም በዚህ አገልግሎት ሰውን በመስጠት፣ በማንኛውም አቅርቦት ሲተጋ አይተነዋል። ዛሬም እንደ እግዚአብሔር ሕዝብ ራእይ የአንድ ሰው ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር እንደሆነ አውቀን ራእዩን የራሳችን አርገን ባለቤት እንሁን። ለራእይ መኖር ትልቅ ስኬት ነው። ስለዚህ በአንድነት ስንሰበሰብ እንደ ባለራእይ እንጂ እንደ ምህመን መሆን የለብንም። ለጋራ ራእይ ስንሰራ የግል ራእይ ይወለዳል። ለቤትህ፣ ለልጆችህ፣ ለትውልድ ባለራእይ ያደርግሃል። ይህ ሲገባን በነህምያ ትውልድ እንደሆነው ሁሉ በቅጥሩ ላይ ሆኖ ይሰራል። የእግዚአብሔር ራእይ ወደ ፍፃሜው ይደርሳል። እግዚአብሔር ይደሰታል፤ የእግዚአብሔር ደስታ ሀይላችን ይሆናል። ነህምያ 8:10

Share this post
Tags
Archive
Sign in to leave a comment